“የውሃ እሴት/ዋጋ” ላይ ያተኮረው ይህ ፕሮጀክት በአዋሽ ወንዝ ላይ በሚገኘው ንዑስ ተፋሰስ እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2024ዓ.ም. እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋነኛነት የበለጠ ውጤታማ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር እና ያለውን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማሰራጨትን ዓላማ አድርጎ ይሰራል፡፡ በአዋሽ ወንዝ ያለው የውሃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ይገኛል፣ የዚህም ዋናው ምክንያት ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ለኢንዱስትሪ እና ለመስኖ እርሻ ስለሚውል ነው፤ በዚህም መነሻ የወንዙ የታችኛው ክፍል በሂደት ሊደርቅ ይችላል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በተፋሰሱ የሚገኙ ህዝቦች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ውሃው አይደርሳቸውም፤ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ያህል ውሃ ወደ ይዞታቸው የመሳብ አቅም አላቸው፣ በአንፃሩ አነስተኛ ገበሬዎች ይህን ለማድረግ አቅም አይኖራቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያለውን ውሃ ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተጠቀምንበት አይደለም፣ ለአብነት በላይኛው የአዋሽ ተፋሰስ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ለመስኖ የሚውል ቢሆንም ውጤታማ አጠቃቀም ግን አይስተዋልም፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ፕሮጀክት በሶስት ዋና ዋና መሶሶዎች ማለትም የውሃ አቅርቦት፣ የውሃ ተደራሽነት እና የውሃ አጠቃቀም ላይ መሰረት ያደርጋል፡፡ በእነዚህ ሶስት ምሶሶዎች ከሚከናወኑ ተግባራት በመቀጠል ፕሮጀክቱ “በውሃ እሴት/ዋጋ” ላይ ተመስርቶ ከውሃ መጠቀም ክፍያ መሰብሰብ የሚቻልበትን የገቢ ሞዴል ያስተዋውቃል፡፡ በመጨረሻም በንዑስ ተፋሰሱ ውስጥ የተሻለ የውሃ አስተዳደር እንዲኖር በሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡
አራቱ ፓኬጆች
ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ፡ የአየር ንብረት፣ የውሃ ከፍታ መጠን፣ የውሃ ጥራት እና ከወንዙ የሚወሰደውን ውሃ መጠን መለኪያና መረጃዎችን መሰብሰቢያ መሳሪያ በወንዙ ላይ ተቀምጠዋል፤
የውሃ መጠቀም ገቢ አሰባሰብ: በውሃ መጠቀም ላይ የክፍያ ስርዓት በመተግበር እና ፍቃድ በመስጠት የበለጠ ተጠቃሚ የሆኑ አቅም ያላቸው ደንበኞች ለሚጠቀሙት ውሃ ክፍያ እንዲፈፅሙ ይደረጋል፡፡ ይህም የጥገና ስራዎችን በተሻለ መንገድ ለማከናወን በቂ ገንዘብ ያስገኛል፤ አርሶ አደሮች በውሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት እንዲደራጁ ይደረጋል፣ እነዚህ ማህበራትም የሚቀርብላቸውን ውሃ በአነስተኛ ክፍያ ያገኛሉ፡፡
ውሃ ማሰባሰብ እና መልሶ መጠቀም: በወንዙ አቅራቢያ ለሚገኙ ተጋላጭ ለሆኑ አካላት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፣ የውሃ አጠቃቀማችንን ለመቀነስና ውሃን በአግባቡ ለመያዝ እንዲሁም መልሶ ለመጠቀም በሌሎች አካባቢዎችም የዝናብ ውሃን ለማሰባሰብ ያሉትን አቅሞች በማስተባበር የሚሰራ ይሆናል፡፡
ውጤታማ የመስኖ ልማት: “በውሃ ተጠቃሚዎች ማህበራት” ውስጥ የሚገኙ አርሶ-አደሮች ውጤታማ የመስኖ አጠቃቀም እንዲኖራቸው እና ምርታማነታቸው ለማሻሻል የሚያስችላቸው ስልጠና ያገኛሉ፡፡
ትብብራዊ አሰራር
በዚህ ፕሮጀክት ወርድ ኤንድ ዳድ ከሌሎች ስድስት አጋሮች ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ሲሆን ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለመቀየር መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን እና የኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የሚሳተፉ ሲሆን የውሃ አስተዳደር ተግባራትን ለማከናወንና ከውሃ አጠቃቀም ገቢ እንዲሰበስቡ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ከውሃ መጠቀም ገቢ መሰብሰብን በተመለከተና የውሃ ጥራት ላይ ክትትል ለማድረግ የሚያስችሉ ፈጠራ ላይ የተመሰረቱ ቴክኒኮችን ለመጠቀም እንዲቻል ኢጀክለካምፕ እና ቨነጊ የተባሉ ሁለት ካምፓኒዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የደች የውሃ ባለስልጣን እውቀትን በማሻገር አጋር ሆኖ የሚሰራ ይሆናል፡፡ ይህን ፕሮጀክት ወርድ ኤንድ ዳድ የሚመራው ሲሆን የደች የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ፕሮጀክት የሚሳተፍ ይሆናል፣ ለፕሮጀክቱ የሚሰበሰበውን በጀት አንድ ሶስተኛ ይሸፍናል፡፡